News and Press

ፀደይ ባንክ እና የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት በጋራ ለመሥራት ተፈራረሙ፡፡

ፀደይ ባንክ እና የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ኤጀንሲ በጋራ ለመሥራት ዛሬ ሐምሌ 09/2016 ዓ.ም በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ተፈራርመዋል፡፡

በፀደይ ባንክ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የዲጂታል እና ብራንች ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ታደሠ፣ ባንኩ ከ14 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እና ከ620 በላይ ቅርንጫፎች ያሉትና በመላ ሃገሪቱ ሰፊ ተደራሽነት ያለው መኾኑን ገልፀዋል፡፡

ስምምነቱም በውክልና የሚተዳደሩ የሰነድ መረጃዎችን ባንኩ ፈጣን እና ተደራሽ በኾነ መልኩ በቀላሉ ለማግኘት እንደሚያስችለው ገልፀዋል፡፡ የባንኩን አገልግሎት በማዘመን እና የደንበኞችን እርካታ በመጨመር በኩል ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀሚድ ካኒሶ፣ ተቋሙ ከፀደይ ባንክ ጋር የተፈራረመው ስምምነት ሐሰተኛ ውክልናን እና ከሰነድ ማጭበርበር ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን ለመከላከል እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡

ስምምነቱ ከሰነዶች ጋር በተያያዘ ሊፈጠር የሚችልን የባንኩን ደንበኞች እንግልት ከማስቀረት ባሻገር አሠራርን ለማቀላጠፍ እንደሚያስችልም ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ፀደይ ባንክ ከ12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ካፒታል እና ከ56 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ሀብት ያለው ግዙፍ ባንክ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *