ፀደይ ባንክ ድጋፍ ለሚሹ ሕጻናት ግማሽ ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የትምሕርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡
ፀደይ ባንክ ግማሽ ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ድጋፍ ለሚሹ 500 ተማሪዎች 500 ደርዘን ደብተር እና 50 ፓኬት እስክርቢቶ ድጋፍ አድርጓል።
ሰውን በሚያስቀድሙ ማኅበራዊ ኀላፊነቶች የሚታወቀው የሁሉም የሆነው ፀደይ ባንክ በበርካታ ዘርፎች ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡
ባንኩ 500, 000 ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ በማድረግም ከዝግባ የሕፃናት እና የአረጋዊያን በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች 500 ደርዘን ደብተር እና 50 ፓኬት እስክርቢቶ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በድጋፍ መርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የፀደይ ባንክ ኮርፖሬት ማርኬቲንግ እና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ቢራራ በዜ (ዶክተር) ባንኩ የሁሉም ባንክ መሆኑን በተግባር እየኖረ የሚገኝ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
ከገንዘብ በፊት ለሰው መድረስን በማስቀደም በርካታ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ያስታወሱት ዳይሬክተሩ ከዚህ ቀደም ለዝግባ የሕፃናት እና የአረጋዊያን በጎ አድራጎት ድርጅት የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ በማድረግ ደጋፊ እና ጧሪ ላጡ ሕጻናት እና አረጋውያን አለኝታነቱን በተግባር ማሳየቱንም አስረድተዋል፡፡
የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ስለሺ ጌታቸው ፀደይ ባንክ ሰውን በማስቀደም እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡ ከዚህ ቀደሙ በተጨማሪ ዛሬ ያደረገው ድጋፍም ደጋፊ ያጡ ሕፃናት ለነጋቸው ተስፋ እንዲያደርጉ እና በርትተው እንዲማሩ የሚያበረታታ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ ፀደይ ባንክ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን በማስቀደም በበርካታ ዘርፎች እያደረገ ያለው ድጋፍም የሚያስመሰግነው ስለመሆኑ አቶ ስለሺ ተናግረዋል፡፡
ፀደይ ባንክ በየዓመቱ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ በማድረግ በተለያዩ ዘርፎች ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ የሚገኝ የሁሉም ባንክ ነው፡፡
Leave a Reply