News and Press

ፀደይ ባንክ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ጋር የክፍያ አጋርነት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡

ፀደይ ባንክ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ዛሬ ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱ ፀደይ ባንክ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የሚሰጠውን የክፍያ እና የርክክብ ስርዓት ለማቀላጠፍ እንዲሁም በመጋዝን ደረሰኝ ብድር ተጠቃሚነት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው፡፡

የስምምነቱን ፋይዳ በተመለከተ የፀደይ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ መኮንን የለውምወሰን እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንድምአገኝ ነገራ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የፀደይ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ መኮንን የለውምወሰን ባለሥልጣኑ አገልግሎቱን እያቀረበላቸው ያሉት አርሦ አደሮች እና አምራች የማኅበረሰብ ክፍሎች ወደ ምርት ገበያው መጥተው ምርታቸውን ሲሸጡ የገበያ መድረኩን ለማመቻቸት እና ብድር ለማቅረብ ባንኩ በጋራ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የውጭ ንግድ አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ ፀደይ ባንክ በተነሳሽነት እንደሚሠራም አቶ መኮንን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንድምአገኝ ነገራ “ከፀደይ ባንክ ጋር ያደረግነው ስምምነት የክፍያ እና የርክክብ ሥርዓቱን ተደራሽ ከማድረጉም ባሻገር የአርሦ አደሮችን የፋይናንስ ተደራሽነት ይበልጥ ያረጋግጣል” ብለዋል፡፡ 

ፀደይ ባንክ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ሃብት፣ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ካፒታል እና ከ9 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል ያለው ግዙፍ ባንክ ነው፡፡

ከ627 በላይ በሚሆኑ ቅርንጫፎቹም በመላ ሃገሪቱ ከ14 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የቁጠባ እና ከ1 ሚሊዮን በላይ የብድር ደንበኞችን እያገለገለ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *