News and Press

በሞባይል ባንኪንግ ከሚፈጸሙ ማጭበርበሮች ይጠንቀቁ!

የሳይበር ምህዳር ይዟቸው ከመጣቸው መልካም አጋጣሚዎች መካከል በየዕለቱ ለምናደርጋቸው ግብይቶች ክፍያ ለመፈጸም ጥሬ ገንዘብ ከመጠቀም ይልቅ በዲጂታል የክፍያ ስርዓት መፈጸም ማስቻሉ ነው፡፡

በሞባይል የባንኪንግ አገልግሎት መጠቀም በጣም ምቹ፣ ቀላል፣ እና አዋጭ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዲጂታል የክፍያ አማራጮች ቀላልና ለአጠቃቀም ምቹ የመሆናቸውን ያህል በጥንቃቄ መጠቀም ካልቻልን ለአጭበርባሪዎች የመጋለጥ እድላችንን ይጨምራል፡፡

ይህ እውነታ ለባንክ መተግበሪያዎች ሲሆን ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ የደኅንነት ስጋቶችን ክፍተኛ ያደርገዋል።

አጭበርባሪዎች ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ የማብጭበርበሪያ መንገዶች ምን ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

  • ከባንክ ነው የደወልንልዎት የሚሉ የማጭበርበርያ ጽሑፎች እና የስልክ ጥሪዎች፣
  • አካላዊ የስልክ ስርቆት እና ምንተፋ፣
  • የፋይናንስ አገልግሎቶችን ማጭበርበር፡- መለያዎን የተዘጋ በማስመሰል በአስቸኳይ እንዲከፍቱ የሚጠይቁ፣ አጠራጣሪ የመለያ እንቅስቃሴን እንደታየና እንዲያረጋግጡ የሚጠይቁ እና ሌሎችንም ተመሳሳይ ሀሰተኛ ማጭበርበርያዎች ሊደርስዎት ይችላሉ፣
  • ሀሰተኛ የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያዎች፣
  • የሞባይል ገቢ ማረጋገጫ ማጭበርበሪያዎች፡- ገንዘብ ከባንክ ገቢ እንደተደረግልዎ የሚገልጽ ሀሰተኛ መልእክት ወደ ሞባይልዎ ወይም ኢ-ሜይልዎ ሊልኩ ይችላሉ፣
  • የእርስዎን ሲም ካርድ ሊቀይሩ ይችላሉ፡- ሲም ከተቀየረ መለያዉ በሌላ አካል ቁጥጥር እንዲውል ያደርጋል፣
  • የባንክ ገንዘብ ዝውውር ማረጋገጫን አስመስለው የተሰሩ የዝዉዉር ማረጋገጫ የጽሁፍ መልዕክት፣ ስክሪንሾት፣
  • የባንክ አካዎንት ወይም ከክፍያ ስርዓት ጋር የተገናኘን ሲም ካርድ በመስረቅ ገንዘብዎን መውሰድ እና ሌሎችንም በየጊዜው የሚፈጥሯቸውን የማጭበርበሪያ ስልቶች ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡

መከላከያ መንገዶች

  • ሞባይላችን (የመገልገያ መሳርያችንን) መቆለፍ፡- በተለይም ግብይቶች በምንፈጽምበት ጊዜም ይሁን በማንኛውም ጊዜ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ መያዝ፤ በጠንካራ የይለፍ ቃል ወይም በባዮሜትሪክ አማራጮች መቆለፍ፣
  • ግብይቶች (ክፍያዎች) ስንጨርስ ከክፍያ መተግበሪያዎች (ዌብሳይቶች) ዘግተን በመውጣት የይለፍ ቃላችን እነሱ ላይ ሴቭ አለመሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፣
  • የባንክ ሒሳቦቻችን ሁኔታ (ታሪክ) በየጊዜው መፈትሽ/መመልከት፣ ማንኛውንም የሞባይል ባንኪንግ ግብይቶች በነፃ ዋይፋይ አለመፈፀም፤ ሁሌም ሞባይል ዳታ መጠቀም፣
  • ባለ ሁለት ደርዝ ማረጋገጫ /Two-factor or Multi-factor Authentication/ ተግባራዊ ማድረግ፤ ወደ ባንክ ሒሳብዎ ከመግባትዎ በፊት የአንድ ግዜ ይለፍ ቃል ወደ ስልክዎ ወይም የኢሜይል አድራሻ እንዲላክ ማድረግ፣
  • የሞባይል ባንኪንግ መተግበርያዎቻችን ማዘመን፡- የሞባይል ባንኪንግ ይሁኑ ሌሎች ሞባይላችን ውስጥ የምንጭናቸው መተግበሪያዎች ወቅታዊ ዝማኔዎች ማድረግ እንዲሁም ከታማኝ ምንጮች አውርዶ መጠቀም፣
  • በባንክ ድረ-ገፆች ላይ የተቀመጡ የደኅንነት መመርያዎችን መከተልና መተግበር፤ ሞባይላችን ላለመጠቀም ወይም ለሌላ ሰው ለመስጠት ስንወስን የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያውን እና ታሪኩን ማስወገድ እና ሚስጥራዊ መረጃዎች ማጥፋት፣
  • ወደ የሞባይል ባንክ አካውንታችን ከመግባታችን በፊት ውጤታማ እና የዘመነ ጸረ-ቫይረስ አንቲስፓይዌር ሶፍትዌር እና ፋየርዎል እንዳለን ማረጋገጥ፣
  • ስልካችንን ለመክፈት እና የባንክ መተግበሪያዎችን ለመክፈት የተለያዩ የፒን ቁጥሮችን (የይለፍ ቃል) መጠቀም፣
  • የሞባይል ባንኪንግ የይለፍ ቃሎች ወይም ፒኖች በስልክ ላይ Save (ሴቭ) አድርጎ አለማስቀመጥ፤
  • ሀሰተኛ የክፍያ ማረጋገጫ የጽሑፍ መልዕክቶችን መጠንቀቅ፡- የሽያጭ ክፍያ በሚፈፀምበት ጊዜ ገንዘቡ ወደ ባንክ ሒሳባችን በትክክል መግባቱ/አለመግባቱ ወደ ባንክ ሂሳባችን በመግባት ማረጋገጥ። ክፍያ እንደተፈፀመ በማስመሰል ተመሳስለው የተሰሩ መልእክቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ መጠንቀቅ፤ ለምሳሌ ሰዎች እቃ ከኛ ሲገዙ ክፍያው በባንክ/ሞባይል ክፍያ መንገድ እንደከፈሉ በማስመሰል የእነዚህ የክፍያ ማረጋገጫ መልእክቶችን በማስመሰል ለማጭበርበር ሊሞክሩ ይችላሉ በመሆኑም መልዕክቶቹ ትክክለኛ መሆናቸዉን ማረጋገጥ፣
  • ደንበኞች ግብይት(ክፍያዎች በሚፈፅሙበት ግዜ ወድያውኑ ክፍያ) ግብይት እንደፈፀሙ የሚያሳውቁ መልእክቶች ወደ ስልካቸው እንደደረሳቸው ማረጋገጥ፣ እነዚህ መልእክቶች በተለያየ ምክንያቶች እክል ገጥሟቸው ሳይደርሱ ሲቀሩ የባንክ አካውንታቸው በመግባት ሒሳብዎን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፣ በሌላ አባባል የባንክ ሂሳብዎን እና ግብይቶችዎን ገብተው እስካልፈተሹ ድረስ የክፍያ ማረጋገጫው የሚገልፅ የጽሑፍ መልእክት ሁሉ ህጋዊ/እውነተኛ ነው ብለው አያስቡ፡፡
  • የሚጠቀሙባቸውን ሲም ካርዶች በይለፍ ቃል መቆለፍም ይገባል፡፡

                     ምንጭ፡- የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *