News and Press

ፀደይ ባንክ አጠቃላይ ሃብቱ 56 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታዎቀ፡፡

መስከረም 14/2015 ዓ.ም በይፋ ወደ ባንክነት የተሸጋገረው ፀደይ ባንክ የባለአክሲዮኖች 3ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ታኅሳስ 20/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኃይሌ ግራንድ ሆቴል አካሂዷል፡፡

የባንኩ የዳይሬተሮች ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አገኘሁ ተሻገር ባቀረቡት ሪፖርት ፀደይ ባንክ በሂሳብ ዓመቱ ማጠናቀቂያ ላይ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘቡ 34 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መድረሱንና ከደንበኞቹ 9 ነጥብ 6 ቢሊዮን ተቀማጭ ብር መሰብሰቡን ገልፀዋል፡፡ ይህም ካለፈው የሂሳብ ዓመት የ39 በመቶ እድገት እንዳለው ነው የተመላከተው፡፡ ፀደይ ባንክ 37 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ብድር ከ 935 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች አሠራጭቷል፡፡ የግብርናውን ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ እየደገፈ የሚገኘው ባንኩ በሂሳብ ዓመቱ ካሰራጨው ብድር ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘውም ይህ ዘርፍ ነው፡፡

እንደ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢው  ሪፖርት ባንኩ በሂሳብ ዓመቱ ካለፈው ዓመት በ30 በመቶ እድገት በማሳየት 6 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ ሲያገኝ በሌላ በኩል ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 49 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጓል፡፡ ለአዳዲስ ቅርንጫፎች ማስፋፊያ እንዲሁም ለቋሚ ንብረት እና ለቴክኖሎጂዎች ግዥ የተመደቡ ወጪዎች፣ የደመወዝ እና ጥቅማጥቅም እንዲሁም የወለድ ክፍያ መጨመር ለወጪው ከፍ ማለት ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ፡፡

የባንኩ አጠቃላይ ሃብት 56 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት የ12 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወይም የ27 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ ግዙፉና ለዘመናት ታማኝነትን ያተረፈው ፀደይ ባንክ ደንበኞቹን ቁጥር ደግሞ 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን አድርሷል፡፡

ባንኩ በሂሳብ ዓመቱ ከግብር በፊት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ማትረፉም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ፀደይ ባንክ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ብቻ 90 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት እስከ ሂሳብ ዓመቱ ማጠናቀቂያ አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ወደ 560 አሳድጓል፡፡

ተደራሽነቱን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ የሞባይል እና ኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ባንኩ የኤቲኤም ማሽኖችንም በተለያዩ አካባቢዎች በማስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ ከሪያ፣ ድሃብሽል እና ሌሎችም የገንዘብ አስተላላፊ ድርጂቶች ጋር በመሥራትም ከውጭ ሀገራት ገንዘብ ለሚልኩ ደንበኞቹ ምቹ አሠራሮችን እየተገበረ ይገኛል፡፡

የባንኩ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አገኘሁ ተሻገር ፀደይ ባንክ የሽግግር ሂደቱን ውጤታማ በሆነ መልኩ በማስኬድ እና ፈታኝ ሀገራዊ ሁኔታዎችን በመቋቋም አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል። ለዚህም የቦርድ አባላት፣ የባንኩ መሪዎች እና ሠራተኞች፣ ብሔራዊ ባንክ፣ የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ፣ የምንጊዜም ታማኝ ደንበኞቹ እና ሌሎችም አጋሮች ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

በሂሳብ ዓመቱ ለሰው ሃብት ልማት ትልቅ ትኩረት በመስጠት 11, 986 የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች በተለያዩ ዘርፎች ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉንም ተናግረዋል።

በቀጣይም የባንኩን ተደራሽነት በቴክኖሎጂ እና በቅርንጫፎች ማስፋፋት፣ አዲስ አበባ የሚገኘውን የባንኩን ባለ 37 ወለል የዋና መሥሪያ ቤት  ሕንፃ ግንባታ ማጠናቀቅእና ሌሎችንም ዐበይት ተግባራት እንደሚከናወኑ አብራርተዋል።

በበርካታ ዘርፎች የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ የሚገኘው ፀደይ ባንክ ባለፈው ዓመት ብቻ ለተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች 200 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የ50 ሚሊዮን ብር፣ ከ12ኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ደግሞ የ600 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉ ይታዎሳል፡፡

ጠቅላላ ጉባኤው ባንኩን ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚያገለግሉ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትንም መርጧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *


Feedback

    Copyright © 2023 Tsedey Bank S.C. | All Rights Reserved